top of page
Writer's pictureEthiopian Writers

አጥላው ወልደ ዮሐንስ

Updated: Apr 14

ግለታሪክ የደብረ ሊባኖስ ጭፍጨፋ

"ከቤት መውጣት የማይችሉትን ደካሞችና ዓይነ፟፟_ስውሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ በሽተኞች እዚያው አሉበት ፈጇቸው እየተባለ ሲወራ ሰማን።

ከዚህ በኋላ መነኩሳቱና ደብተሮቹ የተሳፈሩበት መኪና ብዛት ስፍራውን አጥቦት ስለነበር ተንቀሳቅሶ ጉዞውን ጀመረ። ካንድ ሰዓት በኋላ ተማሪዎቹ የተሳፈሩበትም ካሚዬን ተከትሎ ከገዳሙ አምስት ኪሎ ሜትር ከሚርቅ ጫጋል ከሚባል ስፍራ አቆመ። እዚያም ሁለቱ ሰዓት በኋላ ከቆዩ በኋላ ከቀደም ብሎ የተሳፈሩትን 650 የሚሆኑ መነኮሳትና ደብተሮች ወደ ፍቼ ከተማ አቅራቢያ እለተ ማርያም ከተባለው ስፍራ ወስዶ ወዲያውኑ በመትረየስ ፈጅቷቸው ኖሮ መጽሐፍቶቻቸውንና በደም የተለወሰ ካባና እንደጋቢ ያለ ልብሳቸውን ከፊታችን በተነው።


እኛም ማለቃቸውን ስለተረዳን ካሁን አሁን ይፈጁናል በማለት ስንጠባበቅ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ቆይቶ ካሚዩኑ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ ቀጠለ። ሌሊቱን ሲሄድ አድሮ ሲነጋጋ ደብረ ብርሃን ከተማ ደረሰን።" ከመፅሐፉ የተቀነጨበ።


ፀሐፊው አጥላው ወልደ ዩሐንስ እንዴት እንደተረፉ መፅሐፉን ያንብቡ።

ልጅ ሆኜ አያቴ ስለግራሲያኒ ጭካኔ የሚያወራዉን ዛሬ በደብረ ሊባኖስ ለቤተክርስቲያን ትምህርት ሄደው ከጭፍጨፋው በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈው የፃፉትን መፅሐፍ ኖሮ ባነበብኩለት አልሁ።

እኔ ለአያቴ የመጀሪያዉ የልጅ ልጁ በመሆኔ ለአያቴ በጣም ቅርብ ነበርኹ። ሁሌም በእድሜ ከፍ ካሉ ጓደኞቹ ጋር ከመደብ ላይ ቁጭ ብለው በዚያኔ ከመጀመሪያው ወንድ ልጁ የተበረከተችለት ፊሊፕስ ሬዲዮ ከፍተው የዶቼቬሌንና የተለያዩ ጣቢያዎች እየቀያየረ ያደምጡ ይወያዩ ነበረ። ልጅ በመሆኔ ለእጃቸው ለብ ያለ ውሃ ሴት አያቴ አዘጋጅታ አያቴንና ጓደኞቹን አስታጥብና እነሱ እንጀራ በድቁስ በርበሬ ሲሰጣቸው ለኔ ቁራሽ ተሰጥቶኝ አጠገባቸው እቀመጥ ነበረ። ጓደኞቹ ዜናቸውን አድምጠውና ጠላቸውን ጠጥተው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ አያቴ ስላለፈው ህይወቱ ያጫውተኛል።

አያቴ በስጋ ከተለየን ወደ አስራ አራት አመት ሆኖታል። ነገር ግን ዛሬም አጠገቤ ያለ ያህል ድምፁም ምክሩም ሃይለኛነቱና የዋህነቱ አብሮኝ እለት በእለት እኖረዋለሁ። እወደውም ነበረ በጣም እጅግ በጣም ሩህሩህም ነው። ሴት አንጀት የሚሉት አይነት።

አያቴ በዚያች ፊሊፕስ ሬዲዮ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ተቀምጦ የሚያዳምጡት ስለ እስራኤል እና ፍልስጤም ጦርነት እና ስለተለያዩ እገር ዜና ሲሆን የሚወያዩበት ርዕስ ደሞ ስለ ናዚ ጀርመን ፣ ስለ አለፈዉ ግራሲያኒዉ የደብረ ሊባኖስ የጭካኔ ጭፍጨፋ ፣ ስለ ጣሊያን ጦርነት እና የመሳሰሉትን ነበረ። በተለይ አያቴ ትውልዱ በደብረ ሊባኖስ አካባቢ ስለነበረ ሁሌም ስለግራሲያኒ ጭካኔ ያወራ ነበርና ምናለ ልጅ ባልነበርኩ ያኔ የመጠየቅ እና የማወቅ ጉጉቴ በእድሜዬ ባልተገደበ ኖሮ እያልሁ እቆጫለሁ። ሆኖም በደብረ ሊባኖስ ለቤተክርስቲያን ትምህርት ሄደው ከጭፍጨፋው በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈው የፃፉትን መፅሐፍ ሳገኝ የኋሊት መልሶኝ አያቴን እንዳስታውስ አደረገኝና አይኖቼ በእንባ ተሞሉ።


የየካቲቱ የግራሲያኒ የጭካኔ ጭፍጨፋ የአይን እማኝ ከሆኑት #አጥላው_ወልደ_ዩሐንስ መጽሓፍ ማግኘትና ማንበብ ችያለሁ።

Recent Posts

See All

댓글


bottom of page