ዜሮ ጓደኛ
በደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ by Fikremarkos Desta
አንድ ጊዜ የማስተማሪያ ክፍለ ጊዚያቴን ጠብቄ ሄድሁና፤
"ሲስተር ዛሬ ያለው የማስተማር ጊዜዬ በሌላ ጊዜ እንዳካክሰው
ይፍቀዱልኝ። ምክናያቱም ዛሬ ማስተማር አልችልም"
አልኳቸው።
"ለምን?" አሉኝ እንደዘበት።
"ከጓድኞቼ ጋር በማይረባ ጉዳይ ስንጨቃጨቅ ስለቆየን
ከፍቶኛል" አልኳቸው።
ፈገግ ብለው የመማሪያ መጽሐፉንና ትንሿን የድምጽ መቅረጫ
አንስተው ወደ መማሪያ ክፍላችን ሲሄዱ በግርምታ ተከተልኳቸው። ከዚያ
ቦታቸው ላይ ተቀመጡ ፤ መጽሐፋቸውን ከፈቱ... እየከበደኝ ማስተማር
ጀመርሁ።
አንድ ሰዓት ሲሞላ 'የሻይ' ሰዓታችን ስለሆነ አቆምን።
"አሁን ምን ይሰማሃል?" አሉኝ።
"ስለ ምን?"
"ቅድም ስሜትህ ጥሩ እንዳልነበር ነግረኧኝ ነበር"
"አዎ! - አሁን ግን ረሳሁት" አልኳቸው ፤ እንደገና ፈገግ ብለው፤
"ሲከፋህ ሥራ - ሥራበት! ራስህን በሥራ በመጥመድ ካለህ
የመከፋት ስሜት በቀላሉ መውጣት ትችላለህ፤ አሁን ሻይ
ለማምጣት ከመሄዴ በፊት አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ስንት
ጓደኞች አሉህ?" አሉኝ፤
ልመልስ ስሰናዳ፤
"ተረጋጋ መጀመሪያ፤ ከዚያ ደግሞ ዐይንህን ጨፍነህ አስብ"
ብለውኝ ሄዱ።
ጥያቄው ቀላል ስለነበር ትኩረት ሳልሰጠው ጠበኳቸው። ሻዬንና ብስኩት
ሰጡኝና ለራሳቸው የቀዱትን ሻይ ፉት ብለው፤
"ስንት ጓደኞች አሉህ?" አሉኝ ተመቻችተው እየተቀመጡ።
መቁጠር ጀመርሁ ከዚያ፤
"ከአስር በላይ ጓደኞች አሉኝ" አልኳቸው።
ከት ከት ብለው ሳቁብኝ።
"ለምን ሳቁብኝ?"
''ገረመኛ! ወይ አንተ እጅግ የታደልህ ሰው ነህ፤ ካለበለዚያ ደግሞ የጓደኝነት
ትርጉሙን ገና አታውቅም ማለት ነው። ስለዚህ
ጥያቄዬን ትንሽ ላብራራልህ፤ ችግር ቢገጥምህ ከጎንህ የሚቆም፤ አንደ ራሱ አድርጎ የሚያይህ ... ስንት ጓደኝ አለህ?" ብለው
ፊታቸው ቅጭም አለ።
የተባለውን መስፈርት የሚያሟላ ጓደኛ ለማግኝት ቁጥር መቀነስ ጀመርሁ፤
በመጨረሻም ዜሮ ላይ ደረስሁ። እሳቸው ባሉት ስሌት ጓደኛ የለኝም፤
እኔም እንደዚያ ዓይነት ጓደኝነት ውስጥ ገብቼ አላውቅም። ስለዚህ ድንግጥ
ብዬ፤
"ያሉት ዓይነት ጓደኛ የለኝም" አልኳቸው - ኅፍረት እየተሰማኝ።
እጆቼን በሁለት እጆቻቸው ይዘው፤
"አይዞህ እውነቱ ይህ ነው፤ አብዛኞቻችን እንደራሱ አድርጎ
የሚያየን ጓደኛ የለንም። ምናልባት ጥቂቶች እድለኞች አንድ
ወይም ሁሉት ጓደኛ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል። ሶቅራጠስ፤
ሸክስፒር፤ እየሱስ ክርስቶስ እንኳን ... ተከታይ እንጂ ጓደኛ
አልነበራቸውም" አሉኝ።
ትልቁ ማወቅ እንኳን ከሌላው ከራስ ብዙ አለመጠበቅ ነው፤ ያን ጊዜ
የነጻነት ጎህ ይቀዳል! እውነተኛው ጓደኝነትም ያኔ ይጀምራል! የዚህ ሚስጥር
የገባኝ ግን ከዘመናት በኋላ ነው - ትላንት።
Comments