አዳም ረታ Adam Reta
እትዬ ቢፍቱ አጭር፣ ቀጭን፣ እንደ ጋሸበ ጤፍ የሚሰራው ረዥም ነጭ ጸጉር ያላቸው ወይዘሮ ነበሩ። ከሌሎች ተከራዮች የበለጠ እትዬ ቢፍቱ ለእኔ እና ለፍኖት፣ በትክክል ለፍኖት ያዳሉ ነበረ። ሁልጊዜ ሲመሽ ከፍኖት ጋር ቀጥሮ የሚያሰራንን የክልል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እያማን ናዝሬትን በሚያምሰው የጎሳ ፓለቲካ እያሾፍን፣ እጅለእጅ ተያይዘን በነጫጭ መንገዶች ላይ የጋሪ ፋንድያ በእግራችን እየመታን፣ በጥቁር ሰማይ ላይ የተነሰነሱትን ከዋክብት እየቆጠርን፣ ሙዝ እየበላን (አንዳንዴ እራታችን እሱ ነው) ሲመሽ አውራ ጎዳና ጉብታ ላይ ወጥተን የምታበራ ጋቢ የመሰለች ናዝሬትን እናያለን። በላይዋ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደ አሞራ መብረር እያለምን (መአት ጊዜ እሷ)፣ በስሜት ዱቄት ሆነን አርፍደን ሆቴላችን እንመለሳለን። ሙዙ ካላጠገበን ፍኖት ከእትዬ ቢፍቱ የከሰል ማንደጃ ተውሳ ከሰራችው ሽሮ የተረፈ ካለ ቀዝቃዛውን እየተገባበዝን እንበላለን። ብዙ ጊዜ አያሰኘኝም። አልጋ ጠርዝ ተቀምጣ፣ በጭኖቿ መሃል አስራ ከያዘችው መሰባበር በጀመረ ደረቅ እንጀራ ወጥ እየጠረገች ስትበላ ሁለመናዋ አሳዛኝ ይሆናል። እዛና እዛ የተከፈቱ አጥንታም ቅልጥሞቿ፣ በተለያየ አቅጣጫ የቆመው ሚዶ የማያርመው አንፋሮ የመሰለ ጨብራራ ፀጉሯ (ሁሌ የላብና የአቧራ ጠረን ያለው) ቀጫጭን ረጃጅም ክንዶቿ የሆቴሉ መብራት መደብ ሆኖ የማየው ጠቅላላ ዛላዋ ተስሎ ያላለቀ የእርሳስ ንድፍ መስሎ ትዝ ይለኛል።
ትንሽ የገንዘብ ችግር እንዳለብን እትዬ ቢፍቱ ያውቃሉ። አንዳንድ ጊዜ እኛን ሳያስፈቅዱ የክፍላችንን በር ከፍተው ገብተው ያማረ እራት ያስቀምጡልናል። ሳንግደረደር እንበላለን። ሲነጋ እናመሰግናቸዋለን። 'አይ እናንተ ይህችም ቁም ነገር ሆና' ይሉና ሌላ ምስጋና ላለመስማት ይሸሹናል። ቅዳሜና እሁድ ከክፍላችን ሳንወጣ አንሶላችንን አሸርጠን፣ ራስጌና ግርጌ ተቀምጠን፣ ሙዚቃ እየሰማን፣ ጉንጮቻችንን በሉሉ ጎብበው ለሰአታት እናወራለን ለሰአታት እንላፋለን። አንዳንዴ ከመሃል ፍኖት ልጅነቷ ሲናፍቃት መሰለኝ እተቀመጥንበት እማግልገሌን ታጫውተኛለች። ትን እስኪለን እንስቃለን። ከሁሉ አይነት ዘፈን የአዝማሪ ትወድ ነበረ። ከቴፕ ወይም ከሬዲዮ ማዳመጥ ሲሰለቻት፣ ወይም እኔን ለማዝናናት ብዙ ጊዜ ደስ ያላትን አንዱን አዝማች ከአየር ላይ ጠልፋ በማያስከፋ ድምፅዋ ታንጎራጉራለች፡ ናና ያገሬ ልጅ ናና የወንዜ ልጅ ......ወዘተ......
የስንብት ቀለማት
ከገጽ 196
Comments