እመቤት መንግስቴ
ገፅ 84-85
ሞገስ መታመሙን እንጂ አሁን ምን አይነት ቦታ ላይ እንዳለ አላውቅም። እሱ ጋር ከመድረሴ በፊት ግን ሊላቸው ይችላል ብዬ ያሰብኳቸውን ነገሮች ሁሉ መደርደር ጀመርኩ።
እንዲህ አድርገህ ጎድተኸኛል ብዬ ልወቅሰውና ራሴን ላክም በማልችልበት ሰዓት እሱ ስላልፈለገው ይቅርታ መጠየቁ ምን ይባላል? የውስጤን ትግል አድኜዋለሁ ብዬ ካሰብኩት ህመም በልጦ ያስለቅሰኝ ጀመር። ራስ ወዳድ እንደሆነ አውቃለሁ። ራሱን ወዶ፤ ሌላ ሴት መርጦ፤ ሌላው ቢቀር ምክንያቴ ይኼ ነው ብሎ ሳይናገር፤ ሳንጣላ፤ ክፉ ደግ ሳንነጋገር፤ ሳንኳረፍ እንደወጣ የቀረ ሰው፤ እሱ መዳን በፈለገበት ሰዓት፤ ስለተመቸውና ስለመሰለው ስለ'ኔ ስቃይ ደንታም ሳይሰጠው ይቅርታ መጠየቁ ምን ይባላል?!
ይኼንን እንዲቀማኝ በፍጹም አልፈቅድለትም። ይኼ ይቅርታ እሱ ብቻ የሚድንበት መሆን የለበትም። ይቅር የምለው የአመረቀዘውን ቁስሌን አክሜ፤ ለጥያቄዬ ሁሉ መልስ አግኝቼ፤ ጥፋተኝነቱን አምኖ ነው። ከዚህ ፍንክች አልልም ብዬ ወሰንኩ። ከራሴ ጋር የገጠምኩትን ንትርክ ጨርሼ ስመለስ ራሴን ከሆስፒታሉ በር ላይ አገኘሁት።
Comments