ከደራሲ አዲስ አለማየሁ
ደህና-- ነኝኮ! አይ--- አይ--ዞሽ ደህ---ና ነኝ! ነይ እ--ዚህ ተቀመጭና ደ--ግፊኝ!" አለ በዛብህ:: አንዳንዱን ቃል መጨረስ ልክ እንደ ክፉ ዳገት አድክሞት እመሃከል ላይ እያቋረጠ እያረፈ:: ከዚያ አልጋው ላይ ወጥታ እያለቀሰች ደግፋው ተቀመጠች:: ወይዘሮ የሽመቤት ምንም እንኩዋ የበዛብህና የሰብለን ታሪክ በሙሉ ባያውቁ የዚያንለት ሁኔታቸውን በማየት ብቻ ስቅቅ ብለው አለቀሱ:: ትንሽ ቆይተው ቀሚስና ኩታ ሰጡዋትና ልብስዋን ለወጠች::
ወደ ማታ በዛብህን የተሻለው መሰለ:: ሰብለን ለመቀበል የቀረውን የሀይል ትርፍራፊ የቀረውን የህይወት እንጥፍጣፊ ከያለበት አንድ ላይ እንዳጠራቀመ ሁሉ በርታ ያለ መሰለ! እህልም ከመሰንበቻው የተሻለ በላ:: በተከታዮቹ ሁለት ቀኖች ሲያስነሱትም ሆነ ሲያስተኙት ራሱ ጭምር እዬረዳ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ከሰብለ ጋር እየተጫወተና ለመሳቅም እየሞከረ ለልብዋ የተስፋ ጮራ ሲያሳዬው ሰነበተ:: ከዚያ በሶስተኛው ቀን እንደገና መድከም ጀመረ:: የሀይል ትርፍራፊ የህይወት እንጥፍጣፊ አንድ ላይ ቢጠራቀም ትንሽ ሊያቆይ ይችል እንደሆነ እንጂ ያኖራል አይባልም! የፍርፋሪ ፍርፋሪ የንጥፍጣፊ እንጥፍጣፊ የለውም! ያልቃል! አለቀ! በተገናኚ ባምስተኛው ቀን ደግፋው እንደ ተቀመጠች እቅፍዋ ላይ አረፈ::
.
.
.
ከመፅሀፉ የተወሰደ
Comments